አርሰናል ከፒኤስጂ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አርሰናል በሜዳው ኤሚሬትስ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የፈረንሳዩን ክለብ ፒኤስጂን ያስተናግዳል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በሩብ ፍጻሜው ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜው ሲበቃ ፒኤስጂ በበኩሉ የእንግሊዙን አስቶንቪላ በድምር ውጤት በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀሉ ይታወሳል።
ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚ ቡድኖች በታሪካቸው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሳክተው አያውቁም።
በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል በሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለመቆየት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ተጠባቂ ነው።
የፈረንሳይ ሊግ ኧ ዋንጫን በዚህ የውድድር ዘመን አስቀድሞ ማሳካት የቻለው ፒኤስጂ ተጨማሪ ዋንጫ ለማግኘት የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል።
ኤሚሬትስ ስታዲየም ላይ የሚደረገውን ተጠባቂ ጨዋታ ስሎቬኒያዊው የ42 ዓመት ዳኛ ስላቭኮ ቪንቺክ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል፡፡
ዋና ዳኛው በዚህ ዓመት በሻምፒየንስ ሊጉ የሊግ ቅርጽ ውድድር አርሰናል ፒኤስጂን ኤሚሬትስ ላይ 2 ለ 0 ያሸነፈበትን ጨዋታ መምራታቸው የሚታወስ ነው፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ