Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ክልል በተሻለ የሰላምና ልማት ጉዞ ላይ ይገኛል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ የሰላም እና ልማት ጉዞ ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት÷በክልሉ ተፈጥረው የነበሩ የሰላምና የጸጥታ ችግሮች በዋናነት ከፖለቲካዊ ጽንፈኝነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡

በዚህም ጽንፈኛ ቡድኖች በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ሰብዓዊ፣ ቁሳዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት ማድረሳቸውን አንስተዋል።

በወቅቱ አመራሩ በሚጠበቅበት ልክ ችግሩን ታግሎ በማስተካከል ረገድ ለዘብተኛ አቋም እንደነበረው ጠቅሰው፥ አሁን ላይ በክልሉ ሰላምን በማስፈን ረገድ ማህበረሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ነዋሪዎችም የጽንፈኛ ቡድኑን ትክክለኛ ማንነት ተገንዝበው ከመንግስት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላም የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ እንደሚገኙ ነው የገለጹት፡፡

በአሁኑ ወቅት ክልሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ የሰላምና የልማት ጉዞ ላይ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ በመንግሥት በኩል ሁለት የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን አስረድተዋል።

የመጀመሪያው ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት መሆኑን ገልጸው÷ በዚህ ረገድ መንግስት ዘወትር ለሰላም በሩን ክፍት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።

በሌላ በኩል የቀረበውን የሰላም ጥሪ በመተው የክልሉን ሰላም ለማወክ በሚሰሩ ጽንፈኛ ቡድኖች ላይ መንግስት ሕግ የማስከበር ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ ሕዝብ በቀጣይ ሰላምን በማስጠበቅ በኩል ከመንግስት ጎን በመሆን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.