ኢትዮጵያ የስታርት አፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል እየሆነች ነው – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ትብብር የስታርት አፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል እየሆነች ነው ሲሉ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካን ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት “ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025” የአፍሪካ የትምህርት፣ አይሲቲ እና ክህሎት የሚኒስትሮች ስብሰባ “በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት” በሚል መሪ ሀሳብ ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
በስብሰባው “ለኢኖቬሽን እና ትምህርት ሽግግር የዲጂታል ቴክኖሎጂን አቅም መገንባት” በሚል የሚካሄደውን የፓናል ውይይት ያስጀመሩት በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፤ ስብሰባው የበለጸገችና በቴክኖሎጂ ያደገች ሀገር ለመገንባት ወሳኝ ሁነት መሆኑን ገልጸዋል።
በአፍሪካ የዲጂታል ክህሎት እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አቅምን በማሳለጥ ልማትና እድገትን ማቀላጠፍ እንደሚያስችል አንስተው፤ ወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ማስታጠቅ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት፤ ኢትዮጵያ በትብብር በመስራት ሁሉንም የፈጠራ አቅሞች በመጠቀም ለወጣቶች ምቹ የዲጂታል ስነ ምህዳር ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቁመዋል።
አፍሪካን በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ወጣቶችን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ ትምህርቶች ማብቃት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ያልተቋረጠ ጥረት እያደረገች እንደሆነ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በመንግስትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ጥረት የስታርት አፕ እና የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል እየሆነች ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ስታርት አፕን ለማሳደግ የፖሊሲ ዝግጅት እያደረገች መሆኑን ማብራራታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።