Fana: At a Speed of Life!

ከ70 በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ፍንዳታ ‘በቸልተኝነት’ የተከሰተ ነው – ኢራን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ70 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሕልፈት ምክንያት የሆነው በሀገሪቱ ግዙፍ የንግድ ወደብ ላይ የደረሰው ከፍተኛ ፍንዳታ ‘በቸልተኝነት’ የተከሰተ መሆኑን ገለጸ።

አደጋው የተከሰተው ለኢራን ባለስቲክ ሚሳዔል ጥቅም ላይ የሚውል “ሶዲየም ፐርክሎሬት” የተሰኘ ነዳጅ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሳይደረግለት በመያዙ እና በመፈንዳቱ መሆኑን “አምብሬ” የተሰኘው የደኅንነት ተቋም አስታውቋል።

የኢራን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እስከንዳር ሞሜኒ÷ በደቡባዊ ባንዳር አባስ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ሻሂድ ራጃኢ የንግድ ወደብ ላይ የደረሰው ከፍተኛ ፍንዳታ እና የእሳት ቃጠሎ ምክንያቱ ቸልተኝነት እና የደህንነት ፕሮቶኮሎችን አለመከተል ነው ብለዋል።

የኢራን መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ÷ “ሶዲየም ፐርክሎሬት” የተባለው ነዳጅ ለወደቡ መፈንዳት ምክንያት ነው መባሉን አስተባብሏል፡፡

የተጎዳውን አካባቢ የሚያስተዳድረው የወደብ አገልግሎት ልማት ኩባንያ ለእቃዎች አስፈላጊው ጥንቃቄ ባለመደረጉ በቦታው በተደጋጋሚ በስህተት ምክንያት አስከፊ ችግሮች ይፈጠራሉ ሲል ገልጿል።

የፈነዳው እና ቃጠሎ የደረሰበት ጭነት በጉምሩክ በኩል ያልተመዘገበ እና የማይታወቅ ነበር ያለው ደግሞ የሀገሪቱ ጉምሩክ አስተዳደር ነው፡፡

ባሳላፍነው ቅዳሜ በሻሂድ ራጃኢ ወደብ ላይ በደረሰ ከፍተኛ ፍንዳታ እስካሁን ከ70 በላይ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን÷ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸው ተመላክቷል፡፡

ለአደጋው መከሰት ኃላፊነት አለባቸው የተባሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልጻዋል፡፡

በፍንዳታው ምክንያት የወደቡ ሁለት ሶስተኛው ክፍል በመጎዳቱ አካባቢውን ለማጽዳት እስከ ሁለት ሳምንታት ሊፈጅ እንደሚችል መናገራቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.