በሀገራዊ አጀንዳ በጋራ መመካከርና ልዩነትን በውይይት መፍታት ጊዜውን የሚመጥን ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ አጀንዳ በጋራ መመካከር እና ልዩነትን በውይይት መፍታት ጊዜውን የሚመጥን መንገድ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገነዘቡ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን የኮምቦልቻ ሀገር አቀፍ የኢንዱስትሪና ፋይናንስ ኤክስፖን በዛሬው ዕለት በሥፍራው ተገኝተው አስጀምረዋል፡፡
በዚህ ወቅትም የደሴና ኮምቦልቻ ሕዝብ ሰላም ወዳድ በመሆኑ ጊዜውን እና እውቀቱን ለልማትና ብልጽግና እያዋለ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአካባቢው ሕዝብ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በትክክል እየተገበረ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም ለሌሎች አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ብለዋል፡፡
ምርትና ምርታማነትን ይበልጥ ለማሳደግም ማሕበረሰቡን ባሳተፈ ርብርብ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ግጭት ጠማቂዎች ለሕዝብ የሚጠቅም አላማና ፍላጎት የሌላቸው የሀገር እና የሕዝብ ጠላት የሆኑ አካላት ተላላኪዎች ናቸው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ጊዜው በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝና ምርትን በማሳደግ ብልጽግና እውን የሚሆንበት እንጂ ለጥፋት ኋላቀር ጠብመንጃ የሚነገትበት አይደለም ነው ያሉት፡፡
ዘመኑ በሀገራዊ አጀንዳ ላይ በጋራ የመመካከር እና ልዩነትን በውይይት የመፍታት እንጂ ወንድም ወንድሙን በጠላትነት በመፈረጅ ሀገርን ከጠላት ጋር አብሮ ለማድማት የሚሴርበት እንዳልሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ጊዜው የይቅርታ እና የመደመር መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት ትናንት፣ ዛሬም፣ ነገም ለሰላምና ይቅርታ በሩ ክፍት መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
ስለሆነም የክልሉ ሕዝብ ጸረ ሰላም ሃይሎች የያዙትን የጥፋት መንገድ በመተው ሰላማዊ መንገድን መርጠው ሕዝባቸውን እንዲክሱ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በፊት የያዙት መንገድ ትክክል አለመሆኑን በመገንዘብ በሰላማዊ መንገድ የተመለሱ ታጣቂዎችንም አመስግነዋል፡፡
ለጊዜያችን እንወቅበት፤ ጊዜው የማምረቻ እንጂ የመተኮሻ አይደለም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ÷ ሰላማዊ መንገድን በማይመርጡ ታጣቂዎች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ