Fana: At a Speed of Life!

በመንግስት ብልሃት የተሞላበት አካሄድ በትግራይ ክልል የነበረው ውጥረት መርገቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስትና የትግራይ ክልል ህዝብ በክልሉ ተፈጥሮ ለነበረው ውጥረት የሰጡት ብልሃት የተሞላበት ምላሽ አንዣብቦ የነበረውን የግጭት ሂደት ማስቀረት ማስቻሉ ተገልጿል፡፡

መንግስት በክልሉ ግዜያዊ አስተደዳር ውስጥ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲደረግ ያሳየው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ኃይለኪሮስ ረዳኢ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል፡፡

በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት የሁለት አመት የስልጣን ግዜው የተጠናቀቀውን የክልሉን ግዜያዊ አስተዳዳር የስልጣን ዘመን በማራዘም በክልሉ ዳግም አንዣብቦ የነበረውን የግጭት ሂደት በብልሃት ማስቆም የተቻለበት መንገድ የሚደነቅ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሙሉዓለም ተገኘወርቅ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ በትግራይ ክልል ለመጣው ሰላም የህብረተሰቡ ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም ብለዋል።

በክልሉ የነበረው የስልጣን ሽኩቻ ወደ ጦርነት ሊያስገባ የሚያስችል ምልክቶች የታዩበት እንደነበር የገለጹት ኃላፊው፥ በተለይ በህብረተሰቡና በመንግስት በኩል የታየው ትዕግስት አሁን ላይ በክልሉ ሰላምን ማፅናት ያስቻለ ነው ብለዋል።

መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ለተፈጠሩ ግጭቶች መፍትሄ ለማምጣትና ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ሂደት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ጀምሮ ታጣቂዎችን ወደ ሰላም በመመለስ ህብረተሰቡን እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራዎችን ሰርቷል።

አለመግባባቶችና ግጭቶች ረግበው ሰላም እንዲመጣ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፥ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበርና ሰላምን ማፅናት እንዲቻል ሁሉም የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጥሪ ቀርቧል።

በዓለምሰገድ አሳዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.