በአማራ ክልል የተስተጓጎለውን ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ማካካስ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የተስተጓጎለውን ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ማካካስ እንደሚገባ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን በደሴ ከተማ እየገመገመ ነው።
በምክትል ርዕሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አሥተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት÷ በክልሉ ያለው ግጭት በትምህርት ዘርፉ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል።
በበርካታ አካባቢዎች የመማር ማስተማሩ ሥራ ቢኖርም አሁንም በክልሉ ከ4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም ትውልዱን ወደኋላ እንዲቀር እያደረገው ይገኛል ብለዋል።
ልጆቻችን ተወዳዳሪዎች እና ተመራማሪዎች እንዲሆኑ አሁን ብዙ መልፋት ይጠይቃል ያሉት ሙሉነሽ (ዶ/ር)÷ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉትን ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ማብቃት ይጠበቃል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄን በማጠናከር በቀጣይ ዓመት ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ወደ ትምህርት ቤት ያልመጡ ተማሪዎችን ለማምጣት እና ወደ ትምህርታቸው እንዲመለሱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመተባበር የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የተስተጓጎለውን ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ማካካስ እንደሚገባም አመላክተዋል።