የቡልቡላ ፓርክን የማልማት ስራ ሲከናወን ማህበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ አድርጓል – የቦሌ ክፍለ ከተማ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቡልቡላ ፓርክን የማልማት ስራ ሲከናወን ማህበረሰቡ ስራውን በማስተባበር እና በማቀናጀት ከመንግሰት ጎን ከመቆም በተጨማሪ የስራው አካል እንደነበር የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።
የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ ዓለምፀሐይ ሽፈራው እንደ ሀገር ከለውጡ በኋላ ተፈጥሮን በመግለጥ ትላልቅ ስኬት ያመጡ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማን ጽዱ እና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ወ/ሮ ዓለምፀሐይ÷ ቆሻሻ መጣያ የሆነውን ቦታ በማልማት የቡልቡላ ፓርክን መፍጠር ተችሏልም ነው ያሉት፡፡
ከለውጡ በኋላ እንደ ሀገር ያሉ ሃብቶችን በማልማት ረገድ እየታየ ያለው ለውጥ መንግስት ለሰው ተኮር ስራዎች ትኩረት መስጠቱን ማሳያ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ክፍለ ከተሞች የቡልቡላ ፓርክ ልማትን በመጎብኘት ተሞክሮ እየወሰዱ እንደሚገኙም አንስተዋል፡፡
በትብብር እና በመናበብ ከተሰራ ልማትን ማምጣጥ እንደሚቻል የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ÷ ፕሮጀክቱ ከካርጎ እስከ አቃቂ የሚሸፍን መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
የቡልቡላ ፓርክ ብዙ ወንጀሎች የሚፈጸምበት ቦታ እንደነበር በማንሳት አሁን ላይ አካባቢው ሳቢ ከመሆኑም ባሻገር በርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንዲያገኙ ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
የቡልቡላ ፓርክ እና ከቦሌ ካርጎ እስከ አቃቂ ድልድይ ድረስ የ14 ኪ.ሜ የአረንጓዴ ልማት ስራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት በትናንትናው ዕለት ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወቃል።
በአቤል ንዋይ