Fana: At a Speed of Life!

በኮንትራክተር አቅም ማነስ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የታርጫ ጪዳ አስፋልት መንገድ ሥራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በ4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባው የ64 ነጥብ 8 ኪ.ሜ የታርጫ ጪዳ ሎት 3 አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመር ሥነሥርዓት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) እና የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒን ጨምሮ የፌዴራልና ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተጀምሯል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ተጀምሮ በኮንትራክተሩ አቅም ማነስ ምክንያት ተቋርጦ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የሺዋስ ዓለሙ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።

ለክልሉ ህዝቦች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የታርጫ ጪዳ አስፋልት መንገድ ግንባታ ከዳውሮና ኮንታ ዞኖች ባለፈ ከአጎራባች ጅማና ወላይታ ዞኖች ጋር ያለውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር እንደሚያጠናክርም ተናግረዋል።

የመንገዱ መገንባት ለገበያ ልውውጥ፣ ለቱሪዝም ዕድገት፣ ለክልሉ ኢኮኖሚ መነቃቃትና ለአካባቢው ነዋሪዎች አዳዲስ ዕድሎችን የሚፈጥር እንደሆነም ተመላክቷል።

ለመንገዱ ግንባታ 4 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ከፌደራል መንግስት እንደተመደበና በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለቤትነት በመሳይ ኦሊ ጠቅላላ ተቋራጭና በዩኒኮን አማካሪ እንደሚሰራም ተገልጿል።

የታርጫ ጪዳ አስፋልት መንገድ በ2 ዓመት ከ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቀቅ መገለጹንም የቢሮው ኃላፊ አመላክተዋል።

በአድማሱ አራጋው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.