የመምህራንን አቅም በመገንባት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው – ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል እና የመምህራንን አቅም በመገንባት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአፍሪካን ብሬይን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ‘በ21ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካን ማስተማርና ማብቃት’ በሚል መሪ ሃሳብ ለሶስት ቀናት የተካሄደው ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025 ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።
በዚህ አህጉራዊ ጉባኤ አፍሪካውያን በትምህርት፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ፣ በስራ ፈጠራ እና ስታርት አፕ ሪፎርም፣ አቅም ግንባታ እና ስትራቴጂካዊ ትብብር መፍጠር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ ላይ፤ ጉባኤው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመሰረተ ልማትና መምህራን አቅም ግንባታ ላይ ገንቢ ውይይት ተደርጎበታል ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የተነሱ ሀሳቦች የመምህራንን አቅም ለመገንባትና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል ጥቅም ላይ መዋል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ዘላቂና ጥራት ያለው የልጆች ትምህርት ስርዓት ለመገንባት ዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ የአጭርና ረጅም ዘመን እቅድ ሊኖር እንደሚገባ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አፍሪካ በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብ ከሁኔታዎች ጋር መራመድ ካልቻለች ፈተና እንደሚገጥማት አስረድተው፤ ዘመኑን የዋጀ ዝግጅት በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የተመቸች አፍሪካን እውን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ትምህርት የሁሉም ነገር ቁልፍ በመሆኑ በመደበኛ ትምህርት ጥራትና ተደራሽነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በትምህርት መሰረተ ልማት እና መምህራን አቅም ግንባታ ተጨባጭ ስራ ጀምራለች ብለዋል።